የፓተንት መረጃ
- የፓተንት መረጃ ማለት በታተሙ የፓተንት ሰነዶች ውስጥ የሚገኙ ቴክኒካዊ እና ሕጋዊ መረጃዎችን ያመለክታል። እያንዳንዱ የፓተንት ሰነድ ስለ ፈጠራው ዝርዝር መግለጫ (እንዴት እንደሚሠራ)፣ የመብት ወሰን (ሕጋዊ ወሰኑን የሚያስቀምጥ)፣ ዋቢ መረጃዎችን (ሥራ ፈጣሪዎች እና የቀረበበት ቀን) እና ቀደም ብለው ለነበሩ ተመሳሳይ የፈጠራ ውጤቶች ማጣቀሻዎችን ይዟል። በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ የፓተንት ሰነዶች አሉ። በፓተንት ሰነድ ውስጥ ካለው ቴክኒካዊ ይዘት ውስጥ ሁለት ሦስተኛው በሌላ ቦታ የማይታተም በመሆኑ፣ ይህ የፓተንት ስብስብ በጣም የተሟላ የቴክኖሎጂ መረጃ ስብስብ ነው። የፓተንት ሰነዶች በጥሩ ሁኔታ የተዋቀሩ ናቸው፤ ማጠቃለያ፣ ዝርዝር መግለጫ፣ ስዕሎች፣ የመብት ወሰኖች እና ዋቢ መረጃዎችን የያዙ ናቸው። ይህ ደረጃውን የጠበቀ ዝግጅት ፍለጋን እና ትንተናን ያመቻቻል። ፓተንት በቴክኖሎጂ ዘርፍ (በዓለም አቀፍ የፓተንት ምደባን በመጠቀም) የተመደቡ በመሆናቸው፣ ይበልጥ የታለሙ ፍለጋዎችን ማድረግ ያስችላሉ። የፓተንት ሰነዶች ብዙ ጊዜ የፈጠራ ውጤቶችን ተግባራዊ አተገባበር ያሳያሉ። በዚህ አወቃቀር ምክንያት፣ የፓተንት መረጃ ቋቶች በፈጠራ ባለቤት፣ መብት ተረካቢ፣ በምድብ፣ በቁልፍ ቃላት እና በመሳሰሉት) በሁሉም የቴክኖሎጂ ዘርፎች ውስጥ ዝርዝር ፍለጋዎችን ለማድረግ ያስችላሉ። የፓተንት መረጃ ቋቶች ለተመራማሪዎች፣ ለሥራ ፈጣሪዎች እና ለፈጠራ ባለቤቶች እጅግ ጠቃሚ ናቸው። በዘርፉ ያለውን የዕውቀት ደረጃ በመገምገም (የጥረት መደራረብን ለማስወገድ)፣ አዳዲስ አዝማሚያዎችን ለመለየት እና አንድ ፈጠራ ቀደም ብሎ የባለቤትነት መብት የተሰጠው መሆኑን ለመወሰን ይረዳሉ። የፓተንት ጽሑፎችን መገምገም የፈጠራ ባለቤቶች የፈጠራ ሥራቸውን እንዲያሻሽሉ እና ሊኖሩ የሚችሉ የፈቃድ አሰጣጥ ዕድሎችን እንዲለዩ ይረዳል። የፓተንት ገጽታዎች እና ትንታኔዎች ንግዶች የምርምር እና ስርፀት ስልታቸውን እንዲያቅዱ ይረዳሉ። የፓተንት ውጤቶች በመንግስት እና በትምህርት ተቋማት የፈጠራ ደረጃን ለመወሰን ይተነተናሉ። ለፓተንት ፍለጋዎች ነፃ የሆኑ የህዝብ መረጃ ቋቶች አሉ። ለምሳሌ፣ የዓለም አቀፉ የአእምሯዊ ንብረት ድርጅት "ፓተንት ስኮፕ" ከ124 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ እና ሀገር ዓቀፍ የፓተንት ሰነዶችን ለመፈለግ ያስችላል። የሀገራት የአእምሯዊ ንብረት ቢሮዎች (ለምሳሌ፡ ዩናይትድ ስቴትስ የፓተንት እና የንግድ ምልክት ቢሮ፣ የአውሮፓ ፓተንት ድርጅት እና የግል አገልግሎቶች (ለምሳሌ፡ ጎግል) አሉ። "ፓተንት ሌንስ" እንዲሁ ሰፊ የሆኑ ሊፈለጉ የሚችሉ ስብስቦችን ይይዛል። እነዚህ መሣሪያዎች ተጠቃሚዎች የፓተንቶቹን ሙሉ ጽሑፍ፣ ምስሎች እና ሕጋዊ ሁኔታ እንዲያገኙ ያስችሏቸዋል። የዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት እንደ የልማትና ፈጠራ ሥራዎች ምርምር ባሉ ፕሮግራሞች አማካኝነት ታዳጊ አገሮችን የሚደግፍ ሲሆን እነዚህ ፕሮግራሞች ለፓተንት ቢሮዎች እና ተቋማት የላቁ የፓተንት መረጃዎችን እና የፍለጋ መርጃዎችን ያቀርባሉ። ለምሳሌ፣ በልዩ የፓተንት መረጃ ፕሮግራም ስር፣ ብቁ የሆኑ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እና የፓተንት ቢሮዎች የፈጠራ መረጃዎችን ለመፈለግ እና ለመተንተን የተራቀቁ መረጃ ቋቶችን በነጻ ወይም በዝቅተኛ ዋጋ ማግኘት ይችላሉ። እነዚህ ድጋፎች የአካባቢው የፈጠራ ባለቤቶች ዓለም አቀፍ የፓተንት እውቀትን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የኢትዮጵያ የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ባለቤትነት መረጃዎችን በመጠቀም የምርምርና ስርጸት ስራዎቻቸውን ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር ማጣጣም ይችላሉ። የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የፓተንት መረጃን መጠቀምን በንቃት ያበረታታል (ከተቋቋመበት ዓላማዎቹ አንዱ ነው)። ባለስልጣን መ/ቤቱ በፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዴስክ እና በቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ድጋፍ ማዕከል ኔትወርክ በኩል የፓተንት ፍለጋዎችን ያግዛል። ሥራ ፈጣሪዎች እና ተመራማሪዎች ስለ ፓተንት ወይም አዳዲስ ምርቶችን ስለማልማት ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመወሰን በፈጠራ ሂደት መጀመሪያ ላይ የፓተንት ፍለጋዎችን ማካሄድ አለባቸው።