ንግድ ምልክት ምንድን ነው?
- "ንግድ ምልክት" ማለት የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች መለየት የሚያስችል ማንኛውም የሚታይ ምልክት ሲሆን፤ ቃላትን፣ ንድፎችን፣ ፊደላትን፣ ቁጥሮችን፣ ቀለማትን ወይም የዕቃዎችን ቅርጽ ወይም የማሸጊያዎቻቸውን ቅርጽ ወይም የእነዚህን ጥምረት ያጠቃልላል።
የንግድ ምልክት ምዝገባ ጥቅሞች
- የንግድ ምልክትዎን ማስመዝገብ በርካታ ጉልህ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፥ እነርሱም፦
- በምዝገባው በተሸፈነው አገር በሙሉ፥ ከምዝገባው ጋር ተያያዥነት ባላቸው ዕቃዎች/አገልግሎቶች ላይ የንግድ ምልክትዎን የመጠቀም ብቸኛ መብት ያሰጣል።
- ተመሳሳይ ወይም ግራ የሚያጋባ ተቀራራቢነት ያለውን የንግድ ምልክት፥ ለተመሳሳይ ወይም ግራ ለሚያጋቡ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች እንዳይጠቀሙት ወይም እንዳያስመዘግቡ የመከልከል መብትን ይሰጣል። በተጨማሪም የንግድ ምልክት ከተመዘገበ፥ ባልተመዘገቡ መብቶች ላይ ተመስርቶ ክስ ከመመስረት ይልቅ ጥሰቶችን መከላከል ቀላል፣ ጊዜ ቆጣቢ እና አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅ ይሆናል።
- ምዝገባው የፈቃድ ተጠቃሚዎችን እና ልዩ ፈቃድ የተሰጣቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመመደብ እና ለመቆጣጠር ያስችላል። በአንድ አገር ውስጥ የተደረገ የንግድ ምልክት ምዝገባ በሌሎች አገሮች ለሚደረግ የንግድ ምልክት ምዝገባም እገዛ ያደርጋል።
ለመመዝገብ ብቁ የሆኑ የንግድ ምልክቶች
- የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች በግልጽ መለየት የሚያስችል ማንኛውም የንግድ ምልክት ለመመዝገብ ብቁ ይሆናል። የንግድ ምልክት በጥቁር እና ነጭ ወይም በቀለም ሊመዘገብ ይችላል። በጥቁር እና ነጭ የተመዘገበ የንግድ ምልክት በሁሉም የቀለም ውህዶች ጥበቃ ይደረግለታል፤ በቀለም የተመዘገበ የንግድ ምልክት ግን በተመዘገበበት የቀለም ውህደት ብቻ ጥበቃ ያገኛል። ለመመዝገብ ብቁ የሆነ የንግድ ምልክት የንግድ ምልክቱን መለያ ባህሪ የማይቀንሱ ወይም የሌሎችን ሰዎች መብት የማይጥሱ እስከሆኑ ድረስ ጥበቃ የማይደረግላቸውን አካላት ሊያካትት ይችላል።
ለመመዝገብ ብቁ ያልሆኑ የንግድ ምልክቶች
- የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌላው መለየት የማያስችል እንዲሁም የድምፅ ወይም ሽታ የንግድ ምልክት።
- ከሕዝብ ሥርዓት ወይም ከሞራል ጋር የሚጋጭ የንግድ ምልክት።
- የዕቃዎቹን ወይም የአገልግሎቶቹን ዓይነት፣ ጥራት፣ ብዛት፣ የታሰበበትን ዓላማ፣ ዋጋ፣ መልክዓ-ምድራዊ መነሻ፣ ዕቃው የተመረተበትን ወይም አገልግሎቱ የተሰጠበትን ጊዜ ወይም ሌሎችንም የዕቃዎቹን ወይም የአገልግሎቶቹን ባህሪያት ብቻ የሚገልጹ ምልክቶችን ወይም አመልካቾችን ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት።
- ከዕቃው ተፈጥሮ የመነጨን ቅርጽ ብቻ የያዘ፣ ወይም የዕቃውን የቴክኒክ ውጤት ለማግኘት አስፈላጊ የሆነን ቅርጽ ብቻ የያዘ፣ ወይም ለዕቃው ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠውን ቅርጽ ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት።
- ሕዝቡን ወይም የንግዱን ማኅበረሰብ ሊያሳስት የሚችል በተለይም ስለ ዕቃዎቹ ወይም አገልግሎቶቹ መልክዓ-ምድራዊ መነሻ፣ ተፈጥሮአቸው ወይም ባህሪያቸው የተሳሳተ ግንዛቤ የሚፈጥር የንግድ ምልክት።