አነስተኛ ፈጠራ (ግልጋሎት ሞዴል) ምንድን ነው?
- አነስተኛ ፈጠራ (ግልጋሎት ሞዴል) የአዕምሯዊ ንብረት መብት ዓይነት ሲሆን በአብዛኛው "አነስተኛ" ወይም "የአጭር ጊዜ" ፓተንት ሆኖ በነባር ምርቶች ላይ የሚደረጉ ጠቃሚ ማሻሻያዎችን የመሰሉ አነስተኛ ቴክኒካዊ ፈጠራዎችን ይጠብቃል። ሙሉ ፓተንት ለማግኘት ከሚጠየቁት መስፈርቶች ቀለል ያሉ ሕጋዊ ድንጋጌዎች ያሉት በመሆኑ አነስተኛ ፈጠራዎችን በዝቅተኛ ወጪ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስመዝገብ የሚያስችል አማራጭ ነው። ከመደበኛ ፓተንት በተለየ መልኩ አነስተኛ ፈጠራ (ግልጋሎት ሞዴል)መብት በፍጥነት ሊሰጥ ይችላል ምክንያቱም አንዳንድ ሀገራት የጥበቃ መብት ከመስጠታቸው በፊት የአዲስነት ምርመራ አያደርጉም፤ ሆኖም ይህ መሆኑ የጥበቃ መብቱ ደካማ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
- የአነስተኛ ፈጠራ (ግልጋሎት ሞዴል) ዋና ዋና ገጽታዎች፦
- ዓላማ፦ በነባር ምርቶች ላይ ጠቃሚ ማሻሻያ የሚደረግባቸውን ፈጠራዎች ለምሳሌ አዳዲስ የቴክኒክ መሣሪያዎችን ወይም ቁሳቁሶችን ለመጠበቅ።
- መስፈርቶች፦ ፈጠራው አዲስ እና በኢንዱስትሪ ደረጃ ሊተገበር የሚችል መሆን አለበት። "የፈጠራ ደረጃ" መስፈርቱ ከመደበኛው ፓተንት እጅግ የቀለለ ነው።
- የቆይታ ጊዜ፡-ጊዜው ከመደበኛ ፓተንት በጣም ያነሰ ሲሆን በአብዛኛው ለ10 ዓመታት ይቆያል።
- ሂደት፦ ከመደበኛ ፓተንት ይልቅ የመብት ጥበቃ ፈቃዱን ለማግኘት የሚጠይቀው ወጪ አነስተኛ ሲሆን ሂደቱም ፈጣን ነው።