የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ምርቶች የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሚናቸው የላቀ መሆኑ ተገለፀ

የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ምርቶች የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሚናቸው የላቀ መሆኑ ተገለፀ

የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን መስሪያ ቤት የመልክዓ ምድራዊ አመላካች የመጨረሻ ረቂቅ ህግን ለተለያዩ ባለድርሻዎችና አጋር ተቋማት መስከረም 22/ 2018 ዓ.ም አስተዋወቀ።

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመሰል መልክዓ ምድራዊ አመላካች የሚለው ሃሳብ ለኢትዮጵያ አዲስ ሃሳብ ይሁን እንጂ ያደጉት ሃገራት የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ስርዓትን በመዘርጋትና የህግ ማዕቀፍን በማዘጋጀት ከዘርፉ በእጅጉ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ በመክፈቻ ንግግራቸው የጠቆሙ ሲሆን ኢትዮጵያ በግብርና እና በእደ ጥበብ ምርቶቾ ብዙ ሃብት ቢኖራትም የህግ ስርዓቱን ተግባራዊ ባለማድረጓ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል።

የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ፅንሰ ሃሳብ የሚያስገኘውን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ አንፃር በዮርክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፍሰርና የኦንታሪዮ ምርምር ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር ተሻገር ዳኜ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ረቂቅ ህግ ማዕቀፍ ለኢትዮጵያ የግብርናና ዕደ-ጥበብ ምርቶች እሴት መጨመር የተመላከቱትን ነጥቦች ጨምረው ገለፃ አድርገዋል።

የፈረንሳይ የግብርና ምርምር የዓለም አቀፍ ልማት ማዕከል የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ድጋፍ አስተባባሪ ዶ/ር ኮሊን ሌንሴኜ በበኩላቸው የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ምርቶች በተለይም በኢትዮጵያ ጅማ አካባቢ የሚበቅለው ሊሙ ቡና ስላለው ልዩ ጣዕም እና ለመልክዓ ምድራዊ አመላካች ምርትነት አምቅ አቅም ገለፃ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አመላካች ምርቶች እና የህግ ማዕቀፍ የገለጹት የማህበረሰብ እውቀት እና የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ስራ አስፈፃሚ ታደሰ ወርቁ ረቂቅ ህጉን ማዘጋጀት ከተጀመረ ከሁለት በላይ መሆኑንና ገልፀው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተካሄደና በአሁኑ ወቅት ረቂቅ ህጉን ለማስጸደቅ ለሚመለከተው የመንግስት ተቋም ለመላክ የመጨረሻ ዕጥፋት ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህግ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ፍሬው ኃይሉ የረቂቅ ህጉን ጭምቅ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

ከግብርና ሚኒስቴር፣ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ ግብርና ምርምር፣ ንግድ ምልክት ወኪሎች እና ሌሎች አጋርና ባለድርሻ ተቋማት የተሳተፉ ተወካዮች በረቂቅ ህጉ ላይ የበኩላቸውን ግብዓት ከመስጠታቸውም ባሻገር የተለያዩ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን በማንሳት ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራሮችና ከጽሁፍ አቅራቢዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡