ሥልጣን እና ተግባራት
- የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ሥልጣንና ተግባራት ከአስተዳደራዊ ተግባራት አንስቶ እስከ ህግ ነክ የምክር አገልግሎት ሰፊና ዘርፈ-ብዙ ናቸው። እነዚህ ኃላፊነቶች ለአዳዲስ ግኝት አመንጪዎች እና ለፈጠራ ባለቤቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ወሳኝ ናቸው።
- ማመልከቻዎችን መቀበል እና መመርመር፦ ባለሥልጣኑ ለፓተንት፣ ለንግድ ምልክት እና ለኢንዱስትሪያዊ ንድፍ የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን ያስተናግዳል። ማመልከቻዎቹ ለምዝገባ የተቀመጡትን የህግ መስፈርቶች ማሟላታቸውን ለማረጋገጥ መደበኛ እና ይዘትን መሰረት ያደረጉ ምርመራዎችን ያካሂዳል
- መብቶችን መፍቀድ እና መጠበቅ፦ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ተገቢውንና ውጤታማ ምርመራ ካደረገ በኋላ ለአዕምሯዊ ንብረት መብቶቸ ጥበቃ ያደርጋል፡፡እንዲሁም እነዚህ መብቶች ተግባራዊ ሆነው እንዲቆዩ ለማድረግ የእድሳት ሂደቱን ያስተዳድራል
- መንግሥትን ማማከር፦ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ከአዕምሯዊ ንብረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማጥናትና በመተንተን ለፖሊሲዎች እና ለአዳዲስ ህጎች ዝግጅት ለመንግሥት ምክረ-ሀሳብ ያቀርባል። ይህም እንደ ፓሪስ ኮንቬንሽን እና ማድሪድ ፕሮቶኮል ባሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ውሎች ላይ ማማከርን ይጨምራል
- ደንቦችን ማዘጋጀት፦ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ለአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ፣ ጥበቃ እና ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ልዩ ሂደቶችን የሚመሩ ደንቦችን እና መመሪያዎችን የመቅረጽ እና የመተግበር ኃላፊነት አለበት
- የህዝብ ግንዛቤ፦ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አዕምሯዊ ንብረትን በተመለከተ በህዝቡ እና በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖር ያደርጋል። የአዳዲስ ግኝት አመንጪዎች እና የፈጠራ ባለቤቶች መብቶቻቸውን እንዲረዱ እና እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ ለማገዝ ስልጠናዎችን እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን ያካሂዳል
- ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ድጋፍ፦ ባለሥልጣን መ/ቤቱ በፓተንት ሰነዶች ውስጥ የሚገኙ የቴክኖሎጂ መረጃዎችን በማደራጀትና በማሰራጨት አጠቃቀማቸውን ያበረታታል እንዲሁም ተመሳሳይ የፈጠራ ስራዎች እንዳይደገሙ ለመከላከል ይጥራል። በተጨማሪም የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ድጋፍ ማዕከላትን ያቋቁማል እንዲሁም ያስተዳድራል
- ጥሰትን መከላከል፦ ምንም እንኳን ባለሥልጣን መ/ቤቱ ራሱ ውስን የሆነ የህግ ማስከበር ስልጣን ቢኖረውም፣ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር የባለቤትነት መብት ጥሰትን እና ማጭበርበርን በመከላከል ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል
- ግጭት መፍታት፦ ባለሥልጣኑ የአዕምሯዊ ንብረት ትሪቡናል ያለው ሲሆን ይህ ትሪቡናል ባለሥልጣን መ/ቤቱ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶችን ምዝገባ፣ ተቃውሞ ወይም ስረዛን በተመለከተ በወሰናቸው ውሳኔዎች ቅር በተሰኙ ግለሰቦች የሚቀርቡ ይግባኞችን ይመለከታል። በተጨማሪም የግዴታ ፍቃድ እና ከአዕምሯዊ ንብረት ክርክሮች ጋር የተያያዙ ሲቪል ጉዳዮችን ያስተናግዳል።