ለኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ አመልካቾች ለምን ያስፈልጋሉ?
- የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 45%፣ ለሥራ ዕድል 80% እና ለወጪ ንግድ ገቢ 75% አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይህ ሁኔታ መልከዓ ምድራዊ አመልካች ጥበቃ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ያደርገዋል። ተገቢ የሆነ መልከዓ ምድራዊ አመልካች ህግ የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ ባህላዊ እውቀቶችን ለመጠበቅ እና የምርቶችን ዝና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማጎልበት ይረዳል።
ለመልከዓ ምድራዊ አመልካች ጥበቃ ሊጠቀሙ የሚችሉ የኢትዮጵያ ምርቶች
- ይርጋጨፌ፣ ሲዳሞ እና ሐረር ቡና
- እንደ ትግራይ እና ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች የሚመረት ማር
- እንደ ኮንሶ እና ወላይታ ባሉ አካባቢዎች የሚሰሩ የሸክላ እደ ጥበብ ውጤቶች
- ጤፍ
ለመልከዓ ምድራዊ አመልካች ጥበቃ የሚደረጉ ዋና ዋና ጥረቶች
- ኢትዮጵያ በተለይም ቡና፣ ማር እና ቅመማ ቅመሞችን ጨምሮ ለመልከዓ ምድራዊ አመላካች ምርቶች ጥበቃ ትልቅ አቅም አላት። ይሁን እንጂ የሕግ ማዕቀፉን ገና ለማስጸደቅ እየተሰራ ሲሆን በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የኢትዮጵያን ልዩ የግብርና እና የባህል ቅርስ መሰረት ያደረገ መልከዓ ምድራዊ አመልካች ሥርዓት ለመዘርጋት እና ለማጠናከር በንቃት እየሰራ ነው። እየተከናወኑ ያሉት ዋና ዋና ስራዎች የሚከተሉት ናቸው፦
- ለመልከዓ ምድራዊ አመልካቾች የሕግ ማዕቀፍ ማስጸደቅ
- በኢትዮጵያ ቡና ላይ ያተኮረ የሙከራ መልከዓ ምድራዊ አመልካች ፕሮጀክት መተግበር
- ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ከፈረንሳይ የግብርና ምርምር ድርጅት ጋር በመተባበር በመንግስት እና በግል ባለድርሻ አካላት መካከል የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት። ይህ ፕሮጀክት በፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ነው
- መልከዓ ምድራዊ አመልካቾች ለዘላቂ ልማት ያላቸውን ስልታዊ ሚና ለመወያየት ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን እና ባለድርሻ አካላትን ያሰባሰበ ዓለም አቀፍ የትብብር መድረክ እና ኮንፈረንስ ዝግጅት
የመልከዓ ምድራዊ አመልካች ሕግ ከፀደቀ በኋላ የሚጠበቁ ተግባራት
- የኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ አመልካች ሕግ ከፀደቀ በኋላ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ከሕግ ማርቀቅ ወደ ሥራ አስፈፃሚነት እና ደንበኞችን ወደ ማገልገል ሂደት ይሸጋገራል። ይህም የምዝገባ ሥርዓቶችን መዘርጋት፣ አምራቾችን መምራት፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና እንደ ቡና፣ ማር እና ጨርቃጨርቅ ያሉ ከቦታ ጋር የተያያዙ ምርቶችን ለመጠበቅ መልከዓ ምድራዊ አመልካች መብቶችን ማስከበርን ይጨምራል
- መልከዓ ምድራዊ አመልካች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ሥርዓት መዘርጋት (ለመልከዓ ምድራዊ አመልካች ምርቶች ይፋዊ የምዝገባ ስርዓት መፍጠር፣ ለአምራቾች፣ ለህብረት ሥራ ማህበራት እና ለተቋማት ግልጽ የሆነ የምዝገባ ሂደት ማዘጋጀት እና ለተፈቀደላቸው ተጠቃሚዎች የምዝገባ ምስክር ወረቀት መስጠት
- የደንበኞች መመሪያ እና የአቅም ግንባታ (ለአርሶ አደሮች፣ ለህብረት ሥራ ማህበራት እና ለላኪዎች መልከዓ ምድራዊ አመልካች ጥበቃን እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ስልጠና እና ወርክሾፖች ማዘጋጀት፣ የምርት ዝርዝር መግለጫዎችን፣ የምርት ዘዴዎችን እና መልክዓ ምድራዊ ወሰኖችን ለመመዝገብ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ፣ እና መልከዓ ምድራዊ አመልካች ጥበቃ ስላለው ኢኮኖሚያዊ እና ህጋዊ ጥቅም ግንዛቤ መፍጠር
- መልከዓ ምድራዊ አመልካች ምርቶችን መሞከር እና ማስተዋወቅ (ሥርዓቱን በተግባር ለማሳየት የሙከራ ምዝገባዎችን (ለምሳሌ፡ የሲዳማ ቡና፣ ጤፍ፣ ማር) መጀመር፣ የኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ አመልካች ምርቶችን በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ማስተዋወቅ፣ እንዲሁም መልከዓ ምድራዊ አመልካች ምርቶች በውጭ ገበያ ተፈላጊ የምርት ስም እንዲኖራቸው ከንግዱ ዘርፍ ተቋማት ጋር መተባበር
- ክትትል እና ማስፈጸም፡ በምዝገባ አምራቾች መልከዓ ምድራዊ አመልካች መለያዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋላቸውን መከታተል፣ አላግባብ መጠቀምን፣ ህገ-ወጥ ቅጅዎችን ወይም በገበያ ውስጥ የሚፈጠሩ ያልተገባ ውድድርን መከላከል፣ እና መብታቸው ለተጣሰ ደንበኞች ህጋዊ መፍትሄዎችን መፈለግ
- ዓለም አቀፍ ትብብር (የኢትዮጵያን መልከዓ ምድራዊ አመልካች ሥርዓት ከዓለም አቀፍ አእምሯዊ ንብረት ድርጅት እና ከዓለም ንግድ ድርጅት (WTO/TRIPS) ደረጃዎች ጋር ማጣጣም፣ በስምምነቶች እና በሁለትዮሽ ውሎች የኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ አመልካቾች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ማመቻቸት፣ እና ደንበኞች በመልከዓ ምድራዊ አመልካች የተረጋገጡ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ እንዲልኩ ድጋፍ ማድረግ